Monday, May 4, 2020

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ


"ወዳጄ ሆይ! እግዚአብሔር ነዳያንን የሚልክልህ መስጠትን እንድትለማመድ ነው፡፡ ዛሬ በነዳያኑ አድሮ የሚለምንህ ለኋለኛይቱ ቀን ስንቅ እንዲያስቀምጥልህ ወድዶ ነው፡፡ ታድያ ንጉሥ ወደ ቤቱ መጥቶ የሚያባርር ሰው እንደምን ያለ ጎስቋላ ሰው ነው? እንግዲያውስ ነዳያንን ስታይ ወደ አንተ የመጣው ንጉሠ ሰማይ ወምድር ክርስቶስ እንጂ ሰው አይደለምና አትግፋው፡፡ በረከትህንም ከቤትህ አውጥተህ አትሸኘው፡፡"ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
"አንድ ነዳይ አጥብቆ እየለመነህ በቸልታ ትተኸው ስትሔድ እግዚአብሔርን አጥብቀህ በምትለምን ጊዜ ቢተውህ የሚሰማህን አስብ።"ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
"እንደ ሰውነታችን ዕለት ዕለት እንበድላለን፡፡ በጥምቀት ያገኘነውን ልጅነት እናቆሽሸዋለን፡፡ አዲሱን ሰውነታችን ብሉይ እናደርገዋለን፡፡ ነገር ግን ይህን ዕለት ዕለት ማደስ ይቻላል፡፡ አንድ ቤት እያረጀ ቢሄድ እንደ አዲስ እንሠራዋለን፡፡ ክዳኑን፣ ቀለሙን፣ ምንጣፉን እድሳት እናደርግለታለን፡፡ እኛም በኃጢአት ባረጀው ሰውነታችን ላይ እንዲህ ልናደርግ ይገባናል በንስሐ፡፡"ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል፡፡"ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ



የቅዱስ ያሬድ የዜማ ምልክቶች

የቅዱስ ያሬድ የዜማ ምልክቶችና ሚስጥራቸው!
ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ቤተክርስቲያናችን ካፈራቻቸውና ለአገርና ለቤተክርስቲያን ዘመን ተሻጋሪ ጉልህ አስተዋጽኦ ካበረከቱት ሊቃውንት መካከል አንደኛውና በቀዳሚነት የሚጠቀስ አባት ነው። ቅዱስ ያሬድ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምትጠቀምበትን የዜማ ስልት ያረቀቀ ሊቅ ሲሆን እነዚህ የዜማ ሥልቶችም ከሰማይ የተቀበላቸው ሲሆኑ ግእዝ፣ ዕዝልና አራራይ በመባል ይታወቃሉ። ቅዱስ ያሬድ እነሞዛርትና ቤትሆቭን ከመነሣታቸው ከሺህ ዓመታት አስቀድሞ ተፈጥሯዊ ዜማን በምልክት የገለጸና የዜማ ሥልቶችን በሥርዓት ያረቀቀ ዕውቅ የዜማ ሊቅ ነው።
ከዜማ ስልቶቹ በተጨማሪ ቅዱስ ያሬድ የተለያዩ መጽሐፍትን በመድረስ ለቤተክርስቲያን አበርክቷል። ከደረሳቸው መጽሐፍት መካከልም ድጓ፣ ፆመ ድጓ፣ ዝማሬ መዋሥዕት ወዘተ ይገኙበታል። ሉቁ በድጓ መጽሐፉ ላይ የዐቢይ ፆም ሳምንታትን የየራሳቸው ስያሜ ሰጥቷቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራ ለማሰብ ስምንቱን የዜማምልክቶች በመጽሐፎቹ ላይ አስቀምጧልናል። እነዚህ የዜማ ምልክቶች በቁጥር ስምንት የሆኑበተሰ ዐቢይ ምክንያት ስምንቱ ማኅበረ አይሁድ ተባብረውና መክረው በብዙ ስቃይ ጌታችንን መስቀላቸውና መግደላቸውን ለማሰብ ነው። እነዚህ ማኅበረ አይሁድ የሚባሉትም
፩] ጸሐፍት ፈሪሳዊያን
፪] ሰዱቃውያን
፫] ረበናት (መምህራነ አይሁድ)
፬] መገብተ ምኩራብ (የምኩራብ ሹማምንት)
፭] መላሕቅተ ሕዝብ (የሕዝብ ሽማግሌዎች)
፮] ሊቃነ ካህናት
፯] ኃጥአን እና
፰] መጻብሓን (ቀራጮች) ናቸው።
ቅዱስ ያሬድ ለቤተክርስቲያናችን ያበረከታቸው ስምንቱ የዜማ ምልክቶችም
፩} ይዘት - በአይሁድ ጭፍሮች ለመያዙ (ማቴ 26:50)
፪} ሂደት - ታሥሮ ለመጐተቱ
፫} ጭረት - ለግርፋቱ ሰምበር
፬} ድፋት - የእሾህ አክሊል ለመድፋቱ
፭} ደረት - መስቀል ላይ አንጋለው ደረቱ ላይ ረግጠው ስለመቸንከራቸው
፮} ርክርክ - ስለደሙ ነጠብጣብና አወራረድ
፯} ቁርጥ - በጦር ተወግቶ ፈጽሞ መሞቱ ስለመታወቁ ወይም አይሁዳውያን ጌታችንን ለመስቀል ቁረሰጥ ውሳኔ ስለመወሰናቸው
፰} ቅንዓት - በቅንዓተ አይሁድ ለመገደሉ ምልክቶችና ማስታወሻ ምሳሌዎች ናቸው!
ይሁን እንጂ ቅዱስ ያሬድ ከእነሞዛርትና ቤትሆቨን የቀደመ ሊቅ ሆኖ ሳለ ዛሬም ድረስ ዓለምአቀፋዊ ዕውቅና እንዲኖር ስላልተሠራ በቤተክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ሆኗል። የቅዱስ ያሬድን ሥራዎች ለዓለም በመመስከርና ሊቁን በማስተዋወቅ የኢትዮጵያን ልዕልና ዓለም እንዲያውቀው ለማድረግ እያንዳንዳችን የበኩላችንን መወጣት ይኖርብናል። ይህን ማድረግ የምንችለው ደግሞ አስቀድመን እኛ ሊቁንና ሥራዎቹን ማወቅ ስንችል ነውና ሊቁን እንወቀው። የልዑል እግዚአብሔር ቸርነትና የቅዱስ ያሬድ በረከት ከኹላችን ጋር ይሁን አሜን።
© ዳንኤል ገብረማርያም