Sunday, April 26, 2020

ዳግማይ ትንሳኤ




ዳግማይ ትንሣኤ (ሁለተኛው ትንሳኤ) ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶ ከሙታን ተለይቶ በተነሳ በስምንተኛው ቀን በዕለተ እሑድ ደቀመዛሙርቱ በአንድነት ተሰብስበው ሳሉ ለሁለተኛ ጊዜ ተገልጦ ትንሳኤው ምትሐት ያይደለ ፍጹም አማናዊ እንደሆነና እንደ ቶማስ የተጠራጠረውን ና ንካኝ በማለት ያሳመነበት ዕለት ነው፡፡ዳግማይ (ሁለተኛ) ያሰኘው መገለጡን ይዞ ነው፡፡ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ትንሳኤ ባለፈ የሚመጣውን እሑድ ሰይማ ታከብረዋለች፡፡ /ዮሐ20፤24-30/
ጌታችን ስለምን ዳግመኛ ተገለጠ(
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ ቀድሞ በተዘጋ ግንብ ገብቶ ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሎ ተገልጦላቸው ነበር ዳግመኛም ሐዋርያው ቶማስ ባለበት ተገለጠላቸው ምክንያቱም ደግሞ
1ኛ.ካልዳሰስኩ አላምንም ያለ ሐዋርያው ቶማስን ሊያሳምነው ፡- ቶማስን ደቀመዛሙርቱ መጥተው ጌታችንን በመካከላችን ተገልጦ አየነው ብለው ሲነግሩት ‹‹የችንካሩን ምልክት በእጄ ካላየሁ ጣቱንም ወደ ተቸነከረበት ካልጨመርሁ እጄንም ወደ ጎኑ ካላገባሁ አላምንም ›› ብሎ ነበርና ና ንካኝ ብሎ አሳምኖታል፡፡ቶማስ ለምን ተጠራጠረ ብንል ፈሪሳዊ ስለነበረ ነው፡፡ፈሪሳውያን ትንሳኤ ሙታን የለም ብለው ያምናሉ /በማቴ.ወ22፤23-33/ ሃይ.አበው 48፤8-13 ገጽ255/ እርሱም ከሞት በኋላ ሕይወት አለ ብሎ አያስብም ነበር፡፡የጌታችንን ጎን የነካች የቶማስ እጅ በኋላ ላይ ሳትበሰብስ በሕያውነት ለብዙ ዘመናት ኖራለች፡፡ሀገረ ስብከቱና ሰማዕትነት በተቀበለባት በሕንድ ሀገር ከታቦት ጋር ከመንበሩ ላይ ያኖሯት ነበር፡፡በዓመት በዓመት በእመቤታችን በዓል በአስተርዕ ሊያጥኑ ሲገቡ የሚሾመውን ወጥታ ቀኝ እጁን ትይዘዋለች ዓመት አገልግሎ ያርፋል በዓመቱ ሊያጥን ሲገባ ትይዘዋለች እንዲህ እያለች ትኖራለች፡፡
ሌላው ቶማስን ‹‹ ና ጎኔን ንካ›› ሲለው በኋላ በዓለም ዞሮ ወንጌልን የሚሰብክ ነውና ሐዋርያ ከሆነ ዘንድ ደግሞ ‹‹ሐዋርያት እንዳሉት ጌታችን ተነስቷል›› ብሎ ያስተምር ዘንድ አይገባውም ይልቁንም እንደ ወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹በጆሮአችን የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውንን የተመለከትነውን እጆቻችን የዳሰሱትን እንነግራችኋለን ሕይወት ለእኛ ተገልጻለችና አየናት›› 1ኛዮሐ1፤1-2 እንዳለው ቶማስን ና ንካኝ ብሎታል፡፡በእርግጥ ‹‹ሐዋርያት እንዲህ አለ›› ብሎ ማስተማር ስህተት ሆኖ አይደለም ምክንያቱም እነ ጳውሎስ ጌታችን ሲነሳ አላዩም ግን እንደ ሐዋርያት በዓለም ወንጌልን አዳርሷል ፡፡ነገር ግን ቶማስ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ስለሆነ ግድ ሆኖበታል፡፡
2ኛ.ሰንበትን ሲያጸናልን ፡- የክርስቲያኖች ሰንበት የምንላት ዕለተ እሑድ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ የተነሳባት በመሆኗ የእረፍት የመንግስተ ሰማይ አምሳል ብለን እናከብራታለን፡፡ የዕለቲቱንም ክብርትነት እንድናስብና ዕለተ እሑድ በመጣች ቁጥር ጌታችን የተነሳባትና ለሐዋርያቱ ትንሳኤውን ደግሞ የገለጠባት እንደሆነ እንድናስብ ለአክብሮተ ሰንበት ደግሞ ተገለጠላቸው፡፡አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ‹‹የእሑድ ቀን የክርስቶስ ቀን ናት እሑድ ሰንበትም ተባለች›› መጽ.ምስ ገጽ296
3ኛ.ትንሳኤው ምትሐት እንዳልሆነ ለማስረዳት፡-ጌታችን ራሱ የተገለጠበትን ዓላማ ሲነግራቸው ‹‹እጄን እግሬን እዩ ዳስሱኝም እኔ እንደሆንኩ ዕወቁ በእኔ እንደምታዩት ለምትሐት አጥንትና ሥጋ የለውምና›› ሉቃ24፤39 እንዳላቸው የጌታችን ትንሳኤ ምትሐት ያይደለ አማናዊ በቀደመው ተዋሕዶ ባለመለወጥ እንደተነሳ ለማጠየቅ ተገለጠላቸው፡፡ሲገለጥም በተዘጋ ግንብ መግባቱ መለኮት አለመለየቱንና ወደ ሥጋ መለወጥ እንዳላገኘው ያስረዳል፡፡

No comments:

Post a Comment